8.7 C
London
Sunday, October 26, 2025

Buy now

spot_img

የሰላም፣ የትብብርና የአብሮነት ጥሪ! ከዓለም አቀፍ የኤርትራውያን የይኣክል ንቅናቄ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተላለፈ መልዕክት

ዕለት፡ 30 መስከረም 2025

ዓለም አቀፉ የኤርትራውያን የይኣክል ንቅናቄ፣ በዓለም ዙሪያ በኤርትራ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እንዲሁም የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲረጋገጡ የሚታገሉ ኤርትራውያንን በመወከል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቁ የተሰማውን ጥልቅ ደስታ እየገለጸ፣ ከልብ የመነጨ “እንኳን ደስ አላችሁ” ለማለት ይወዳል። ይህ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሕዝቦችም ያለውን ጠቀሜታ እንገነዘባለን፤ በመሆኑም የግጭት መንስኤ ከመሆን ይልቅ የሰላም፣ የትብብርና የጋራ ብልጽግና ምንጭ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። አዲሱ የ2018 ዓመት፣ ልዩነቶችና ግጭቶች በሰላማዊ ድርድርና በእርቅ የሚፈቱበት የሰላምና የመረጋጋት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ንቅናቄያችን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሊፈነዳ በሚችል አዲስና አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ያለውን ጥልቅ ስጋትና ሐዘን ለመግለጽ ይገደዳል። ላለፉት በርካታ ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር፣ የኤርትራን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚገዳደሩ አደገኛ ዛቻዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን እንገነዘባለን። የዚህ ዘመቻ ዋነኛ ትኩረት የኤርትራ የቀይ ባህር ወደብ የሆነችውን ዓሰብን በኃይል ለመቆጣጠር ያለመ ነው። ይህ አደገኛ አካሄድ ከፖለቲካዊ መግለጫነት አልፎ ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የሚጥስናየቀጠናውን ሰላም ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ድንበር ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ መስተካከል አለበት” ሲሉ በይፋ ተናግረዋል። የቀይ ባህር መዳረሻ ማግኘት “የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ” እንደሆነና ኢትዮጵያ ዓሰብን መልሳ የምታገኝበት የጊዜ ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል። ይህ ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እየተሰራጨ የሕዝቡን ስሜት ለጦርነት እንዲነሳሳ ለማድረግ እየተሠራበት እንደሆነ እንገነዘባለን። ከዚህም ባለፈ፣ የተዛቡ መረጃዎችንና የሐሰት ካርታዎችን በማሰራጨት የጦርነት ስሜትን ለማራገብ እየተሞከረ ነው። ይህ ዓይነቱ ድርጊት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርና የአፍሪካ ኅብረት መመሥረቻ ሕግጋትን በቀጥታ የሚጥስ ነው። እነዚህ ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሁሉንም አባል ሀገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያከብራሉ።

በእርግጥም፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር ለክርክር የሚቀርብ አይደለም። የኤርትራ ድንበሮች፣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ፣ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ወቅት በነበሩት ወሰኖች የተመሰረቱ ናቸው። የድንበር ግጭቱም በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት በቀረበው “የመጨረሻና አስገዳጅ” የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት አግኝቷል። አሁን በኢትዮጵያ በኩል እየቀረበ ያለው የይገባኛል ጥያቄ፣ ይህን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ስምምነት ለማፍረስ ሆን ተብሎ የሚደረግ ሙከራ ነው። በተጨማሪም፣ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ እየተደረጉ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችም እነዚህ ዛቻዎች ባዶ እንዳልሆኑና ጦርነቱ አይቀሬ ሊሆን እንደሚችል ያሳያሉ።

የዚህ ቀውስ መሠረታዊ መንስኤ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚታየው የኃይልና የማስፋፋት አዝማሚያ ሲሆን፣ በኤርትራ ያለው አፋኝ አገዛዝ ደግሞ ለውጥረቱ መባባስ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አገዛዝ፣ ከኢትዮጵያ የሚሰነዘረውን የሉዓላዊነት ስጋት፣ በኤርትራ ሕዝብ ላይ ያለውን አምባገነናዊ ቁጥጥር ለማጠናከር እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀምበታል። ይህ የውጭ ስጋት፣ ሀገሪቱን የማያባራ የጦርነት ዝግጁነት ውስጥ በማስገባት ጨቋኙ ሥርዓት የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እንደ መሣሪያ ያገለግለዋል። የኤርትራ ሕዝብ ላለፉት ሁለት

አሥርት ዓመታት “ጦርነትም ሰላምም በሌለበት” ሁኔታ ሲሰቃይ የኖረ ሲሆን፣ አሁን የተፈጠረው ስጋትም ለአምባገነኑ ሥርዓት ዕድሜን በመቀጠል የሕዝቡን መከራ የሚያራዝም ነው። ኤርትራና ኢትዮጵያ ለብዙ አሥርት ዓመታት በጦርነት ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። አዲስ ግጭት መፈጠሩ በሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች ላይ ከባድ ጥፋት ያስከትላል፤ ገና ያልሻሩ ሥነ-ልቦናዊና አካላዊ ቁስሎችን ይቆሰቁሳል፣ መፈናቀልንና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም ያባብሳል። ከባድ ሰብአዊ ቀውስ በማስከተል የአፍሪካ ቀንድን መረጋጋት ያናጋል፤ ለጽንፈኛ ቡድኖች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ልንቆጣጠረው ወደማንችለው የጸጥታ ቀውስ ሊመራን ይችላል።

ስለሆነም፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ይህን አይቀሬ የጦርነት አደጋ በመቃወም ከኤርትራዊው ወንድሙ ጎን እንዲቆም አስቸኳይ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ሁላችንም የምንጠቀመውና የምንበለጽገው እርስ በእርስ በመጠቃቃት ሳይሆን በመቀራረብ፣ በትብብርና የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅ ነው። ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ የጦርነትን ከባዱን ዋጋ የሚከፍለው ሕዝቡ እንጂ በአራት ኪሎ ወይም በአዲ ሃሎ ያሉ ባለሥልጣናት አይደሉም። ስለሆነም የሁለቱ ሀገራት ሰላም ወዳድ ዜጎች፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና ምሁራን በአንድ ድምፅ ጦርነትን እንዲቃወሙና ለሁለቱ ሕዝቦች ሰላማዊ አብሮ መኖርና የጋራ ብልጽግና እንዲሟገቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በዚህም መሠረት የሚከተሉትን ነጥቦች እናሳስባለን፦

  1. የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት ላይ የሚያካሂደውን የይገባኛል ጥያቄና በኃይል ለመውሰድ የሚያደርገውን ዛቻ፣ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስና ለዓለም ሰላም ስጋት መሆኑን ሁሉም ወገን በጽኑ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን።
  2. በኢትዮጵያ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን (EEBC) የተሰጠው “አስገዳጅና የመጨረሻ” ውሳኔ በሁለቱም ሀገራት በኩል እንደ ይፋዊ ድንበር ሙሉ ዕውቅና እንዲሰጠው እንጠይቃለን።
  3. ጦርነት ቀስቃሽ ወታደራዊ ዝግጅቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና ግጭቶችን ለመቀነስ ወታደሮች ከድንበር አካባቢዎች እንዲርቁ አጥብቀን እንጠይቃለን።
  4. የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ሰፊ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ እንዲጀምሩ እናሳስባለን። ድንበሮችን በኃይል ለመለወጥ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለውና ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል ግልጽ ሊደረግ ይገባል። በዓለም አቀፍ ሕግጋትና በድርድር በሚደረስ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በዓሰብ ወደብ በኩል የባህር በር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የዚህ ዲፕሎማሲ አካል ሊሆን ይችላል።

እኛ ሰላም ወዳድ ኤርትራውያን፣ ይህን የውጭ ስጋት በምንታገልበት ወቅት፣ በኤርትራ ያለው አምባገነናዊ አገዛዝ አፋኝ ፖሊሲዎቹን እንዲያቆምና ሀገራችን ወደ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር እንድታደርግ ትግላችንን እንቀጥላለን።

ዓለም አቀፍ ይኣክል የኤርትራውያን ንቅናቄ
30 መስከረም 2025

Stay Connected

16,400FansLike
745FollowersFollow
2,890SubscribersSubscribe
Prisoner of Consciencespot_img

Latest Articles